3ቱ የክርስቲያን ልብሶች


3ቱ_የክርስቲያን_ልብሶች
|=================|
✍ለማነኛውም ሰው ልብስ መሠረታዊና አስፈላጊ  ነገር መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ለክርስቲያን ደግሞ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ክርስቲያን መልበስ ያለበት እንደ ማነኛውም ዓይነት ሰው ልብስ ሳይሆን ልዩ የሆነ የልብስ ዓይነት አለ፡፡ እነዚህ ልብሶዎች ገበያ ላይ የማይገኙ፣ በገንዘብም የማይገዙ ደግሞ በፍፁም የማይሸጡ ፍፁም ድንቅ  ልብስ ናቸው፡፡
✍በአጠቃላይ የሰው ልጅ ሦስት ዓይነት ልብስ ይለብሳል፡፡ እነዚህም፦
1.ኢየሱስ ክርስቶስን ወይም ሰይጣን ዲያብሎስን
2. አዲሱን ሰው ወይም አሮጌውን ሰውን
3.የእግዚአብሔር ዕቃ ጦርን ወይም የጠላት ዕቃ ጦርን
➊አንደኛው ልብስ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
✍ማነኛውም ሰው ከምንም በላይ በመጀመሪያ ደረጃ መልበስ ያለበት የልብስ ዓይነት ክርስቶስ እንደሆነ የእግዚአብሔር ቃል በበገላትያ 3፥27 ላይ “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።” እያለ ይናገራል፡፡ በሮሜ 13:14 ላይም “ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ።”  እያል በድጋሚ ይናገራል፡፡ ይህን ልብስ ያልለበስ ሰው ሁሉ የለበሰው የሰይጣን፣ የዓለም ወይም የሥጋ ልብስ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሰው ለብሶ የሚዞረው ሞትና ጥፋት ነው፡፡ ቶሎ ኢየሱስ ክርስቶስን በመልበስ የነፍሱን ዋስትና ማግኘት አለበት፡፡

ኢየሱስ ክርስቶሰን መልበስ ማለት ፦
--------------------------------------------
1. በብርሃን መኖር፦ የኢሱስ ብርሃን ነው፡፡
✍ኢየሱስ ክርስቶስን የለበሰ ብርሃንን መልበስ አለበት ምክንያቱም እርሱ ብርሃን ነው፡፡ እርሱን የሚከተለ ሁሉም ብርሃን ነው፡፡ “ደግሞም ኢየሱስ፦ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው።”  ዮሐንስ 8፥12፡፡
✍ኢየሱስን እየተከተሉ በጨለማ መኖር በጭራሽ የማይሆን ነገር ነው፡፡ ብርሃን ባለበት ጨለማ አይኖርም፡፡ “ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት፦ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።” 1ኛ ዮሐንስ 1፥5
✍ክርስቲያኖች የብርሃን ልጆች ስለሆኑ ብርሃን መልበስ፣ በብርሃን መመላለስ አለባቸው፡፡ “ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም፤”  1ኛ ተሰሎንቄ 5፥5 ደግሞ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም።” ማቴዎስ 5፥14
2. በቃሉ መኖር፦ ኢየሱስ ቃል ነው፡፡
✍ኢየሱስ ራሱ ቃል ስለሆነ አንድ ክርስቲያን ይህን መልበስ አለበት፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በዮሐንስ 15: 4፣7 ላይ "በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም..7 በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል" ይላል፡፡
3. በፈቃዱ መኖር
✍ፈቃዱን ማድረግ ወይም መልበስ እንጅ ለላው  ሁሉ ምንም ዋጋ የለም፡፡ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።” ማቴዎስ 7፥21
4. በቅድስና መኖር
✍እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል በቅድስና ጠርቶናልና። 1ኛ ተሰሎንቄ 4፥7፡፡ ስለዚህ ኢየሱስን ለብሶ በኃጢአት መኖር የለም፡፡ “ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።” 1ኛ ጴጥሮስ 1፥15-16
5. በመንፈስ ቅድሰ ፍሬ መኖር
✍ክርስቶስን የለበሰ በክርስቶስ መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራትና በፍሬ መኖር አለበት፡፡ “ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል”ዮሐንስ 15፥8፡፡ ይህ ካልሆነ የእግዚአብሔር ቃል በዮሐንስ 15፡4፣6 ላይ እንደምናገረው ይጠፋል፡፡ "በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም …በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።" እነዚህ ፍሬዎች “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።” ገላትያ 5፥22 ናቸው፡፡
➋ሁለተኛው ልብስ፦አዲሱን ሰው ነው፡፡
••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
✍የእግዚአብሔር ቃል በኤፌሶን 4፥24 “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” ይላል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ከመናገር በፍት በኤፌሶን 4፥22 “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥” ይላል፡፡ አሮጌውን አስወግደን አዲሱን ለምን መልበስ እንዳለብን ደግሞ በቆላስይስ 3፥10 ላይ “የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤” እያሌ ምክንያቱን ያስቀምጣል፡፡
✍ማነኛውም ዓይነት ክርስቶስን የለበሰ ወይም ዳግም የተወለደ፤ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኝ አድረገው የተቀበለ ሰው በመቀጠል መልበስ ያለበት አዲሱን ሰው ነው፡፡ ኢየሱስን እየተከተለ አሮጌውን ልብስ መልበስ በፍፁም አይሆንም፡፡ በአንድ ጊዜ አንድ ሰው የሰይጣንና የኢየሱስን በጋራ መልበስ አይችልም፡፡
✍ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ክፍል "አሮጌ" ስለ ለማለት የፈለገው ፊተኛ፣ የቀድሞ፣ የድሮ፣ የጥንት፣ ያረጀ ማለት ነው፡፡ በለላ በኩለ ደግሞ "ፊተኛ ኑሮ"  ማለት የድሮ ባሕርይ፣ የቀድሞ ምልልስ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ አሮጌውን ሰው አስወግዱ ሲል በአሮጌው ሰው አካሄድ አትሂዱ፣ በአሮጌው ሰው አስተሳሰብ አትመሩ ወይም አሮጌው ሰው ዋጋ ለሚሰጠው ነገር ዋጋ አትስጡ እያለን ነው፡፡
✍የሰው ልጅ አሮጌነትን የተላበሰው በቀዳማዊ አዳም በደል ምክንያት ነው፡፡ ቀዳማዊ አዳም አስቀድሞ በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረ ቅዱስና እና ንፁሑ ባሕር ነበረው፡፡ መተዳደሪያውም ጽድቅና ቅድስና ብቻ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህን እስከ መጨረሻ መጠበቅ አልቻለም፡፡ የሰው ልጅ በኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር ያለበሰውን ክብር ልብሱን አወለቀና አሮጌ ሰው ሆነ( ዘፍ 3)፡፡ ከዚህ በኃላ የሰው ልጅ ባሕርይ ወደ ኃጢአት አዘነበለና የሚወለደውም ሁሉ የኃጢአት ባርያ ሆነ፤ የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ የነበረው የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ከመሆን ራቀና የኃጢአት ማደርያ ሆነ፤ ከእግዚአብሔር ፍቃድ ይልቅ የራሱንም ፈቃድ የሚፈጽም ሰው ሆነ፡፡  ሮሜ 5፡12፡፡
አሮጌው ሰው ምን ዓይነት ሰው ነው?
-----------------------------------------------
★አሮጌው ሰው እግዚአብሄርን የማይፈልግ ለመንፈሳዊ ነገር ዋጋ የማይሰጥ የምድራዊ ወይም ስጋዊ ባህሪ ያለው ሰው ነው፡፡
★አሮጌው ሰአሮጌው ሰው ከእግዚአብሄር ጋር የተጣላ፣ ለእግዚአብሄር የማይገዛ፣ እግዚአብሄርን ሊያስደስት የማይችል ሰው አካሄድ ነው፡፡
 ★አሮጌው ሰው ለእግዚአብሄር ነገር ግድ የሌላው የተፈጥሯዊ ሰው ባህሪ ያለው የስጋ፣ የሃጢያት፣ የክፉ ምኞት ሃሳብ ነው፡፡
★አሮጌው ሰው የአሁን ሰው ብቻ የሆነ ስለ ሰማይ ግድ የለውም አርቆ ሊያይ የማይችልም ሰው ነው፡፡
★አሮጌው ሰው አላማና ግብ የለውንም ህይወት እንደነዳው የሚሄድ ራሱን የማይገዛ ሰው አካሄድ ነው፡፡ መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። ፊልጵስዩስ 3፡19 አሮጌው ሰው "ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ" እንደሚሉት አይነት ሰው ነው፡፡ ስጋ የእግዚአብሄር አላማ ፣ የእግዚአብሄር ፍቃድ፣ ለእግዚአብሄር መኖር፣ ጌታን መከተል፣ ራስን መካድ፣ ጌታን ማስደሰት የሚሉት ነገሮች አይገቡትም አይረዳቸውም፡፡
☞ለአሮጌው ሰው የእግዚአብሄር መንግስት የማይታይ የማይጨበጥ ነገር ነው፡፡ የእግዚአብሄር ነገር ሞኝነትይ ነው፡፡ ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡14
☞ለአሮጌው ሰው ፍቅር ሞኝነት ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው ራስ ወዳድነት የህይወት መንገድ ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው ስግብግብነት ህይወት ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው ትህትና ደካማነት ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው ምህረት ማድረግ አለማወቅ ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው ጥላቻ የህይወት ዘይቤ ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው መስጠት ማካፈል ማባከን ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው ትእቢት ሃያልነት ነው፡፡
✍ እግዚአብሔር ለአዳም የገባለትን ቃልኪዳን የሚፈጸምበት የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ግን እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ባሕርይ ባሕርይ አድርጎ ከድንግል ተወለዶ ይህን አሮጌ ሰውነት አደሰለት ገላ4፡4፡፡ እኛም ሐዋርያው፡-“ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችሁታል” እንዳለን ታደስን፤ ክርስቶስን ለበስን፤ በእኛ ዘንድ የነበረው አሮጌው ሰውም ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ ሞተ ገላ.3፡27፡፡ አዲሱን ልብስ አለበሰ፡፡
✍ይህ ከሆነ ዘንዳ ሐዋርያው ተመልሶ አሮጌውን ሰው አስወግዱት፤ አዲሱን ሰው ልበሱት የሚለን ስለ ምንድን ነው?   ቅዱስ ጳውሎስ “አሮጌውን ሰው አስወግዱ” ሲለን “ድጋሜ ተጠመቁ” እያለን ሳይሆን “በመንፈስ ቅዱስ በሰውነታችሁ ሠልጥኖ ያለውን የኃጢአት ልማድ አስወግዱ” ሲለን ነው፡፡  እርሱም በውስጣችን ላደረው መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ በመታዘዝ የቀድሞውን የኃጢአት ልማዶቻችንን በማስወገድ ክርስቶስን መስለን መገኘታችን ነው፡፡
✍አንድ ሰው ከሰውነቱ የኃጢአትን ፈቃድ አስወግዶ በጽድቅ ሕይወት በመመላለስ በእርሱ እግዚአብሔር መገለጥ ሲጀምር ያኔ ግን “በእውነት አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለብሶታል” ይባልለታል፡፡ ስለዚህ ጥምቀት ኃጢአትን ድል የምንነሣበትን ትጥቅ ታስታጥቀናለች፡፡ ትጥቁን ታጥቀን ኃጢአትን ድል የመንሣቱ ሓላፊነት ግን የእኛ ግዴታ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን መጠመቁ ብቻ አያድነውም፡፡ የሚድነው በጥምቀት ባገኘው፣ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠው ጸጋ ተጠቅሞ እንደ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተመላለሰና አዲሱን ሰው ክርስቶስ ለብሶ በመገኘት ለዚህ ዓለም በመልካም ምግባሩ ብርሃን ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ለመዳን ከእግዚአብሔር ርቀን ለሰይጣን ፈቃዶች በመታዘዝ በሰውነታችን ያለመድናቸውን ኃጢአቶችንና የኃጢአት ፈቃዶችን ለማስወገድ ብንተጋ በውስጣችን ያደረው መንፈስ ቅዱስ አቅም ሆኖን እውነትን እየገለጥን አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለመልበስ እንበቃለን፡፡
የአዲሱ ሰው ልብሶች ምንድ ናቸው?
-------------------------------------------------
✍የእግዚአብሔር ቃል በቆላስይስ 3፡12-14 ላይ የአዲሱ ሰው ልብስ ዓይነት ምን እንደሆነ በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ "እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ … ¹⁴ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።
➌ሦስተኛው ልብስ፦ የእግዚአብሔር ዕቃ ጦር
•••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••••
✍የእግዚአብሔር ቃል በኤፌሶን 6፡10-11 ላይ "በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ። የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። የሰው ልጅ በዓለም ላይ ያለውን ልብስ ሁሉ መልበስ ብችል እንኳን የዲያብሎስ ሽንገላ መቃወም በፍፁም አይችልም፡፡ አንድ ክርስቲያን አዲሱን ማኝነት ይዞ መቀጠል ከፈለገ ይህን ልብስ መልበስ ግድ ይላል፡፡ ስለዚህ ይህ ልብስ ለክርስቲያን እጅግ በጣም አስፈላጊ ልብስ ዓይነት ነው፡፡
✍በዚህ ክፍል ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚናገረው በጌታና በሃይሉ ችሎት ልንበረታ የምንችለው የጌታን ሙሉ ዕቃ ጦር በመልበስ ነው። እንደ እግዚአብሔር ህዝብ፣ የሚጠብቀንና ያለ ቅድመ ሁኔታ የሚወደን ሀያል አምላክ አለን። ነገር ግን በተጨማሪ ሁልጊዜ ወጥመድ የሚያዘጋጅ ጠላትም አለን። ወታደር የተሟላ የጦር ዕቃ ሳይለብስ ወደ ጦር ሜዳ አይወጣም። እኛም የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ስንለብስ የዲያብሎስን ሽንገላ ለመቋቋም እንችላለን። ጠላታችን አይተኛም። ጠላታችን ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ በዙሪያችን እንደሚዞር አንበሳ ነው። ስለዚህ የጠላትን ወጥመድና ሽንገላ ለማፍረስ የነቃንና የታጠቅን መሆን አለብን።
የእግዚአብሔር ጦር ዕቃዎች ወይም ልብሶች ምንድ ናቸው?
----------------------------------------------------------------------------
✍የእግዚአብሔር ቃል በኤፌሶን 6፡13-18 ላይ እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠንን መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ይገልጽልናል። ሐዋርያው ጳውሎስ የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃዎችን አማኞች ራሳቸው እንዲለብሱ ነው የሚነግራቸው:: “...የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ” ቁ. 11 “...የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ” ቁ. 13:: ስለዚህ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ስንል አማኞች በጌታ ሲያምኑ ወዲያ የለበሱትና የታጠቁት ነገር ሳይሆን በዚህ ክፍል ጳውሎስ የሚናገረው አማኞች ራሳቸው መልበስና ማንሳት ስላለባቸው ትጥቆች ነው:: በቁ. 14-17 ላይ አማኞች ሊለብሷቸው የሚገቡ የእግዚአብሔር ጦር ዕቃዎችና ትጥቆች ተዘርዝረዋል:: እነዚህም
❖እንደ ወገብ መታጠቂያ (ቀበቶ) የሆነ እውነት
❖እንደ የደረት ጥሩር የሆነ ጽድቅ
❖እንደ ጫማ የሆነ ወንጌልን የመስበክ ዝግጅት
❖እንደ ጋሻ የሆነ እምነት
❖እንደ ራስ ቁር (helmet) የሆነ ድነት (salvation) እና
❖እንደ ሰይፍ የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው::
የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ማንሳትና መልበስ የአማኞች የዕለት ተለት ኃላፊነት እና ግደታ ነው::
የእግዚአብሔር ጦር ዕቃዎች ወይም ልብሶች ምንን ይወክላሉ?
--------------------------------------------------------------------------------
✍በዚህ ክፍል የተጠቀሰው የአለባበሱ ምሳሌያዊ አገላለጽ የሮማውያን ወታደሮችን አለባበስ የሚያስታውስ ነው:: የሮማውያን ወታደሮች ከራስ ቁር እስከ እግር ጫማ ድረስ የታጠቁትን ሙሉ ትጥቅና በእጆቻቸውም ያይዙአቸውን ጋሻና ሰይፍን ያስታውሳል:: እዚህ ላይ የተጠቀሰው አለባበስ ምሳሌያዊ አገላለጽ መሆኑን መዘንጋት የለብንም:: ለምሳሌ በ1ተስ 5፣8 ላይ እምነትና ፍቅር እንደ ጥሩር፣ የመዳን ተስፋ ደግሞ እንደ ራስ ቁር ተጠቅሰዋል::
✍ስለዚህ የአለባበሱን ምሳሌዎች ስንመለከት በጣም አጥብቀን ማየት ያለብን ሊተላልፍ የተፈለገው መልእክት ላይ እንጂ በግድ መንፈሳዊ እውነቶቹን ከተሰጠው የአለባበስ ምሳሌ ጋር አንድ ለአንድ ማዛመዱ ላይ አይደለም:: በመቀጠል የጦር ዕቃዎች ምኑን እንደሚወክሉ እንመለከታለን፡፡
1) እውነት፦“እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ...” ኤፌ 6:14::
✍እውነትን መልበስ ወይም መታጠቅ ማለት ክፉ ሥራን በመጥላት በጽድቅና እግዚአብሔር በሚወደው መንገድ በየዕለቱ መሄድ ነው፡፡
✍እውነት ከውሸትና ከሐሰት የራቀ ሕይወትን ያሳያል:: የተመሰለውም እንደ መታጠቂያ ወይም ቀበቶ ነው:: ይህ መልእክት በተጻፈበት ዘመን የሰዎች ልብስ ሰፋ ያለ አንድ ወጥ ቀሚስ መሰል ነገር ነበር:: ከቤት ወጥቶ ሊሄድ ወይም አንድን ነገር ለማድረግና እንደ ልብ ጎምበስ ቀና ለማለት የሚፈልግ ሁሉ በመጀመሪያ ወገቡን በቀበቶ ይታጠቅ ነበር:: ያለበለዚያ ወገቡን ሳይታጠቅ በዘርፋፋ ቀሚሱ ሊጓዝ ወይም ሥራ ሊሠራ የሚሞክር ልብሱን ሊረግጥና በራሱ ልብስ ሊጠለፍ ይችላል:: ስለዚህም ወገብን መታጠቅ ተነስቶ አንድን ነገር ለማድረግ የመዘጋጀት ምልክትም ነው፡፡
✍የእግዚአብሔር ቃል በሉቃስ 12፣37 እና በ17፣8 ላይ " እንግዲህ ከእውነት ይልቅ ውሸትን እንደ ዋና መሣሪያ በሕይወቱ የሚለማመድ ሰው በራሱ ልብስ ተጠልፎ እንደሚወድቅ ሰው ይቆጠራል:: እንዲህ ያለውን ሰው ለመጣልና ለማሸነፍ ለሰይጣን በጣም ቀላል ነው:: ምክንያቱም ውሸት የእግዚአብሔር ጦር ዕቃ ሳይሆን የሰይጣን የራሱ መሣሪያ ነውና፡፡ ዮሐ 8፣44 “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።”

2) ጽድቅ፦“የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ” ኤፌ6:14::
✍ጽድቅን መታጠቅ ወይም መልበስ ማለት በጽድቅ የሆነ ሕይወት ላይ ነው ማተኮር ያለብን እንጂ ዋናው ትኩረቱ ጥሩሩ ላይ መሆን የለበትም:: እንግዲህ ጳውሎስ በዚህ ክፍል የሚናገረው ስለሚለበስ እና በውጪም ስለሚታይ ነገር ነው:: ምንም እንኳን በጌታ አማኞች የጸደቁ ቢሆንም፣ በዚህ ክፍል የሚናገርው ግን እንደ ጸደቀ ሰው፣ ጽድቅን በዕለት ተለት ኑሮ መለማመድን ነው:: እንደ ጌታ ልጆች ከክፋት ርቆ በጽድቅ መመላለስን ነው:: ጽድቅ በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛና ደስ የሚያሰኝ ሕይወት ነው::  ጽድቅ አለን፣ እውነት አለን፣ እምነት አለን ወዘተ ማለት ብቻ መልበስን አያሳይም:
✍አማኞች ሁሉ የእግዚአብሔርን ጽድቅ በክርስቶስ ያገኙ ቢሆንም፣ በዚህ ክፍል ግን የሚናገረው ያገኙትን ጽድቅ በሕይወታቸው መለማመድ እንዳለባቸው ነው:: የጸደቀ ሰው ክርስቶስ በውስጡ ያስቀመጠውን የጽድቅ ሕይወት በዕለት ተለት ሕይወቱ ሊያሳየው ይገባል:: ወይም በሌላ አነጋገር የጸደቀ ሰው እንደ ጸደቀ ሰው ሊኖር ይገባዋል እንጂ ጨርሶ ጽድቅ የሚባል ነገር በአጠገቡ እንዳላለፈ ክፉና አመጸኛ ሰው ሊመላለስ አይገባውም:: ስለዚህ ጽድቅን መልበስ ከክፋትና ከአመጻ፣ ፍትሕና እውነት ከሌለው አኗኗር መራቅና ኃጢአትንም መጥላት ማለት ነው:: ያለበለዚያ ግን በክፋትና በአመጻ በኃጢአትም እየኖሩ፣ የዲያብሎስን ሽንገላ ድል አደርጋለሁ ማለት ደረቱ ምንም ሳይሸፈን ለጥቃት እንደተጋለጠ ሆኖ ወደ ውጊያ የሚገባ ወታደርን መምሰል ነው:: በጠላት ላይ እውነተኛ ድል ያለው ወደ ክፋትና ወደ አመጽ የሚያመራውን የሰይጣንን ማታለል ዕለት ተዕለት መቋቋሙ ላይና ጸንቶ እምቢ ማለቱ ላይ ነው እንጂ የጸሎት ፕሮግራም ላይ ብቻ በኃይል መገሠጹ ላይ አይደለም:: እውነተኛው ጦር ሜዳ ላይ ድል እየተነሱና እየተሸነፉ እንዲያው ብቻ መገሠጽ፣ ከባዶ ፉከራነት አያልፍም::
3) የሰላም ወንጌል፦ “በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ” ኤፌ 6:15::
✍ይህ ክፍል ከሁሉም ለመረዳት ከበድ ያለና ግልጽ ያልሆነ ቢሆንም ሃሳቡ ግን ወንጌልን ለመስበክና የምስራቹን ለማውራት ሁል ጊዜ የተዘጋጀን ሕይወት ያሳያል ኢሳ 52፥7:: እንዲህ አይነት ሰው እግሮቹ እንቅፋት እንደማይጎዳቸው በጫማ እንደተሸፈኑ እግሮች ይመሰላሉ:: እግሮቹ ሁል ጊዜ መልካሙን የሰላም ወንጌል ለማድረስ የተዘጋጁ ናቸው እንጂ ክፉውን ለማውራት፣ ለማማትና ለመሳሰሉት የሚሮጡ አይደሉም::
4) እምነት፦ “በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ” ኤፌ 6:16::
✍እምነት በዚህ ክፍል እንደ ጋሻ ነው የተመሰለው:: በሮማውያን ዘመን ይጠቀሙበት የነበረው ጋሻ እኛ በአገራችን ከምናውቀው ክብና አነስተኛ ጋሻ የተለየ ነው:: ጋሻው በቆዳ የተለበጠ ሲሆን ሰውነትን ሁሉ የሚሸፍን ነው:: ከተቃራኒ የሚላኩትን እሳት የተለኮሱ ፍላጻዎች/ቀስቶች/darts ለማጥፋት እንዲችል ቆዳው በውሃ ይነከር ነበር:: ሰይጣን በአማኞች ሕይወት የሚልካቸው መንፈሳዊ ሕይወትን ሊያቃጥሉና ሊለበልቡ የሚችሉ በእግዚአብሔርና በቃሉ ላይ እንዲጠራጠሩ የሚያደርጉ ብዙ ፍላጻዎች አሉት:: እምነት፣ አይሆንም ይሄ የሐሰት ዜና ነው እንድንልና የሚመጣውን ክፉ ሃሳብ እንዳናስተናግድ የሚያደርግ፣ ብዙ ክፉ ሃሳቦችን የሚያከሽፍ ዋና የመከላከያ መሣሪያ ነው:: ሰይጣንም በተቻለው ሁሉ ይህንን ጋሻ አማኞች እንዲጥሉ ይሞክራል ሉቃ 22፣31-32::
5) መዳን/ድነት፦“የመዳንንም ራስ ቁር ... ያዙ” ኤፌ 6:17::
✍ይህ ክፍል ድነት/salvation ሁል ጊዜ በአማኝ ሕይወት ዋና ሚና መጫወት ያለበት እንደሆነ የሚያመለክት ነው:: ድነቱን የጣለና እንደ ዋና ነገር ያልያዘ ሁሉ ራሱን ሳይሸፈን ወደ ጦርነት የገባን ወታደር ይመስላል:: ይህም ለሞት እንደተጋለጠ ሰው መሆን ነው::
6) የእግዚአብሔር ቃል፦“የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው::” ኤፌ 6:17::
✍ከተዘረዘሩት የጦር ዕቃዎች ውስጥ እንደ ዋና ማጥቂያነት የተጠቀሰ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው:: ይህም ከላይ እንደገለጽነው የመንፈሳዊ ውጊያ ዋናው እምብርት መከላከልና ሳይወድቁ መቆም እንደሆነ በይበልጥ ያረጋግጥልናል:: በዚህ ክፍል የተጠቀሰው የእግዚአብሔር ቃል የመንፈስ ቅዱስ ሰይፍ እንደሆነ ተገልጿል:: ማለትም የእግዚአብሔር ቃል በአማኞች ሕይወት ውስጥ፣ በሰገባ እንዳለ ሰይፍ በሙላት ሲኖር፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በሚያስፈልግ ጊዜና ሁኔታ እንደ ሰይፍ እየመዘዘ የጠላትን ክፉ ሃሳብና ፈተና ለመቁረጥ ይጠቀምበታል:: ይህን አይነቱን የመንፈስ ቅዱስ አጠቃቀም ለመረዳት በተለይ የጌታን ፈተና መመልክቱ ይረዳል ማቴ 4፣1-11:: ጌታ በእግዚአብሔር ቃል የተሞላ ስለነበር በሚፈተነው ፈተና ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ለጊዜው የሚያስፈልገውን ቃል እንደ ሰይፍ እየመዘዘ ይሰጠው ነበር:: በዚህም ጠላት ድል ተደረገ::
7) ጸሎት፦“በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፣ በዚህም ሃሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፣ ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፣ ስለ ወንጌል በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንሁ፣ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ::” ቁ. 18-20::
✍ጸሎት ምንም እንኳን እንደሚለበስ መንፈሳዊ ዕቃ ጦር ባይጠቀስም በመንፈሳዊ ውጊያም ይሁን ለአጠቃላይ መንፈሳዊ ሕይወት ሁሉ ዋና ማገርና ምሰሶ ነው:: በዚህ ክፍል በአማርኛው “በጸሎትና በልመናም ሁሉ” የሚለው አባባል በእንግሊዝኛው in all prayer and petition ተብሎ ተተርጉሞአል:: ይህም ሁሉንም የጸሎት አይነት ሁሉ የሚያጠቃልል ነው:: ለግል የሚደረግን ማንኛውም አይነት ጸሎትን (በአዕምሮ ወይንም በመንፈስ/በመንፈስ ቅዱስ/በልሳን የሚደረግን ይሁዳ 20 1ቆሮ 14፣14-15) እንዲሁም ለሌሎች ቅዱሳን የሚደረግ ምልጃንና መማጸንን ሁሉ ያጠቃልላል:: ጳውሎስ አማኞች አንድ አይነት ብቻ ጸሎት ሳይሆን ሁሉንም አይነት ጸሎት ሁል ጊዜ ያለ ማቋረጥ እንዲጸልዩ ነው የሚመክረው:: በተለይ ምልጃን በተመለክተ ከሌሎቹ የጦር ዕቃዎች ሁሉ የሚለየው፣ የግል መከላከያ መሣሪያ ሳይሆን ሌሎች ቅዱሳንን ለማገዝ ለሌሎች የሚደረግ እርዳታ መሆኑ ነው:: ይህም መንፈሳዊ ሕይወትና ውጊያ በግል ብቻ የሚወጡት ነገር ሳይሆን የጋር ትግል እንደሆነና መደጋገፍና መያያዝ እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ነው::

Comments

Popular posts from this blog

መንፈሳዊ አገልግሎት

መንፈሳዊ እርጅና