አድሱን ሰው ልበሱ

አዲሱን_ሰው_ልበሱ፡፡
••••••••••••••••••••
✍የእግዚአብሔር ቃል በኤፌሶን 4፥24 “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” ይላል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ከመናገር በፍት በኤፌሶን 4፥22 “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥” ይላል፡፡ አሮጌውን አስወግደን አዲሱን ለምን መልበስ እንዳለብን ደግሞ በቆላስይስ 3፥10 ላይ “የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤” እያሌ ምክንያቱን ያስቀምጣል፡፡

✍ማነኛውም ዓይነት ክርስቲያን ዳግም የተወለደ፤ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኝ አድረገው የተቀበለ ሰው መልበስ ያለበት ምርጡ ልብስ አዲሱን ሰው ነው፡፡ ሰው ኢየሱስን እየተከተለ አሮጌውን ልብስ መልበስ በፍፁም አይሆንም፡፡ ሰው በአንድ ጊዜ የሰይጣንና የኢየሱስን በጋራ መልበስ አይችልም፡፡

✍ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ክፍል
 ✔"አሮጌ" ስለ ለማለት የፈለገው ፊተኛ፣ የቀድሞ፣ የድሮ፣ የጥንት፣ ያረጀ ማለት ነው፡፡
✔ በለላ በኩለ ደግሞ "ፊተኛ ኑሮ"  ማለት የድሮ ባሕርይ፣ የቀድሞ ምልልስ ማለት ነው፡፡
✍ሐዋርያው ጳውሎስ አሮጌውን ሰው አስወግዱ ሲል
✔በአሮጌው ሰው አካሄድ አትሂዱ
✔በአሮጌው ሰው አስተሳሰብ አትመሩ ወይም
 ✔አሮጌው ሰው ዋጋ ለሚሰጠው ነገር ዋጋ አትስጡ ማለት ነው፡፡

✍የሰው ልጅ አሮጌነትን የተላበሰው በቀዳማዊ አዳም በደል ምክንያት ነው፡፡ ቀዳማዊ አዳም አስቀድሞ በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረ ቅዱስና እና ንፁሑ ባሕር ነበረው፡፡ መተዳደሪያውም ጽድቅና ቅድስና ብቻ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህን እስከ መጨረሻ መጠበቅ አልቻለም፡፡ የሰው ልጅ በኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር ያለበሰውን ክብር ልብሱን አወለቀና አሮጌ ሰው ሆነ( ዘፍ 3)፡፡ ከዚህ በኃላ የሰው ልጅ ባሕርይ ወደ ኃጢአት አዘነበለና የሚወለደውም ሁሉ የኃጢአት ባርያ ሆነ፤ የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ የነበረው የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ከመሆን ራቀና የኃጢአት ማደርያ ሆነ፤ ከእግዚአብሔር ፍቃድ ይልቅ የራሱንም ፈቃድ የሚፈጽም ሰው ሆነ፡፡ “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤” ሮሜ 5፥12

✍ቀድሞ መተዳደሪያውም ጽድቅና ቅድስና የነበረው የሰው ልጅ ባለመታዘዝ ምክንያት በመንፈስ ሞት ሞቴ ከእግዚአብሔር ተለየ አሮጌው ሰው ሆነ።  ነገር ግን በአንዱ መታዘዝ ምክንያት ይህ አሮጌው ሰው ዳግም የቀድሞ ማንነቱን አገኘ። “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ” (ሮሜ 5፥19)። ይህም የሆነው ከበዛልን እግዚአብሔር ምህረትና ፀጋ የተነሳ ነው። “ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ።” ሮሜ 5፥15
✍ እግዚአብሔር ለአዳም የገባለትን ቃልኪዳን የሚፈጸምበት የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ግን እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ባሕርይ አድርጎ ከድንግል ተወለዶ ይህን አሮጌ ሰውነት አደሰለት ገላ4፡4፡፡ እኛም ሐዋርያው፡-“ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችሁታል” እንዳለን ታደስን፤ ክርስቶስን ለበስን፤ በእኛ ዘንድ የነበረው አሮጌው ሰውም ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ ሞተ ገላ.3፡27፡፡ አዲሱን ልብስ አለበሰ፡፡
✍ይህ ከሆነ በድጋሚ ሐዋርያው ተመልሶ አሮጌውን ሰው አስወግዱት፤ አዲሱን ሰው ልበሱት የሚለን ስለ ምንድን ነው?   ቅዱስ ጳውሎስ “አሮጌውን ሰው አስወግዱ” ሲለን “ድጋሜ ተጠመቁ” እያለን ሳይሆን “በመንፈስ ቅዱስ በሰውነታችሁ ሠልጥኖ ያለውን የኃጢአት ልማድ አስወግዱ” ሲለን ነው፡፡  እርሱም በውስጣችን ላደረው መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ በመታዘዝ የቀድሞውን የኃጢአት ልማዶቻችንን በማስወገድ ክርስቶስን መስለን መገኘታችን ነው፡፡
✍አንድ ሰው ከሰውነቱ የኃጢአትን ፈቃድ አስወግዶ በጽድቅ ሕይወት በመመላለስ በእርሱ እግዚአብሔር መገለጥ ሲጀምር ያኔ ግን “በእውነት አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለብሶታል” ይባልለታል፡፡ ስለዚህ ጥምቀት ኃጢአትን ድል የምንነሣበትን ትጥቅ ታስታጥቀናለች፡፡ ትጥቁን ታጥቀን ኃጢአትን ድል የመንሣቱ ሓላፊነት ግን የእኛ ግዴታ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን መጠመቁ ብቻ አያድነውም፡፡ የሚድነው በጥምቀት ባገኘው፣ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠው ጸጋ ተጠቅሞ እንደ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተመላለሰና አዲሱን ሰው ክርስቶስ ለብሶ በመገኘት ለዚህ ዓለም በመልካም ምግባሩ ብርሃን ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ለመዳን ከእግዚአብሔር ርቀን ለሰይጣን ፈቃዶች በመታዘዝ በሰውነታችን ያለመድናቸውን ኃጢአቶችንና የኃጢአት ፈቃዶችን ለማስወገድ ብንተጋ በውስጣችን ያደረው መንፈስ ቅዱስ አቅም ሆኖን እውነትን እየገለጥን አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለመልበስ እንበቃለን፡፡

✍በክርስቶስ ቤዛነት የቀድሞውን ማንነትን ያገኘው ክርስቲያን ዘወትር ይህን አድሱን ሰው ማለትም ክርስቶስን መልበስ አለበት።
-----------------------------------------------
#አሮጌው_ሰው_ምን_ዓይነት_ሰው_ነው?
-----------------------------------------------
★አሮጌው ሰው እግዚአብሄርን የማይፈልግ፣ ለመንፈሳዊ ነገር ዋጋ የማይሰጥ የምድራዊ ወይም ስጋዊ ባህሪ ያለው ሰው ነው፡፡
★አሮጌው ሰው ከእግዚአብሄር ጋር የተጣላ፣ ለእግዚአብሄር የማይገዛ፣ እግዚአብሄርን ሊያስደስት የማይችል ሰው አካሄድ ነው፡፡
 ★አሮጌው ሰው ለእግዚአብሄር ነገር ግድ የሌላው የተፈጥሯዊ ሰው ባህሪ ያለው የስጋ፣ የሃጢያት፣ የክፉ ምኞት ሃሳብ ነው፡፡
★አሮጌው ሰው የአሁን ሰው ብቻ የሆነ ስለ ሰማይ ግድ የለለው አርቆ ሊያይ የማይችል ሰው ነው፡፡
★አሮጌው ሰው አላማና ግብ የለለው ህይወት እንደነዳው የሚሄድ ራሱን የማይገዛ ሰው አካሄድ ነው፡፡ መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። ፊልጵስዩስ 3፡19
★አሮጌው ሰው "ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ" እንደሚሉት አይነት ሰው ነው፡፡ ለእግዚአብሄር አላማ፣ ለእግዚአብሄር ፍቃድ ግድ የማይሉ፣ ለእግዚአብሄር መኖር፣ ጌታን መከተል፣ ራስን መካድ፣ ጌታን ማስደሰት የሚሉት ነገሮች ፈፅመው የማያስብ ሰዎች ናቸው፡፡

☞ለአሮጌው ሰው የእግዚአብሄር መንግስት የማይታይ የማይጨበጥ ነገር ነው፡፡ የእግዚአብሄር ነገር ሞኝነት ነው፡፡ "ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ  ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።" 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡14
☞ለአሮጌው ሰው ፍቅር ሞኝነት ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው ራስ ወዳድነት የህይወት መንገድ ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው ስግብግብነት ህይወት ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው ትህትና ደካማነት ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው ምህረት ማድረግ አለማወቅ ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው ጥላቻ የህይወት ዘይቤ ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው መስጠት ማካፈል ማባከን ነው፡፡
☞ለአሮጌው ሰው ትእቢት ሃያልነት ነው፡፡

-----------------------------------------------
#የአዲሱ_ሰው_ልብሶች_ምንድ_ናቸው?
-------------------------------------------------
✍የእግዚአብሔር ቃል በቆላስይስ 3፡12-14 ላይ የአዲሱ ሰው ልብስ ዓይነት ምን እንደሆነ በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ "እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ … ¹⁴ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።
◆በአጠቃላይ
✔ የአድሱ ሰው ልብስ ክርስቶስ ነው።
 ✔የአድሱ ሰው ልብስ ፍቅር ነው።
✔የአድሱ ሰው ልብስ ቅድስና ነው።
✔የአድሱ ሰው ልብስ ጽድቅ ነው።

Comments

Popular posts from this blog

መንፈሳዊ አገልግሎት

3ቱ የክርስቲያን ልብሶች

መንፈሳዊ እርጅና