በአንዳች አትጨነቁ

#በአንዳች_አትጨነቁ። (ፊልጵስዩስ 4፥6)
▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪
◆በመጽሐፍ ቅዱሳችን በተለይም በአድስ ኪዳን ውስጥ ኢየሱስ ደጋግሞ አትጨነቁ በማለት አማኞች በአንዳችም መጨነቅ እንደሌለባቸው በብዙ ቦታ ተናግሯል። ኢየሱስ በዮሐንስ 16፥33 ላይ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤” እንዳለ ሁሉ በዓለም ሳላችሁ የሚያስጨንቅ ነገር አለ። ይህ ባይኖር ኖሮ ኢየሱስ ደጋግሞ አትጨነቁ አይልም ነበረ። አትጨነቁ ያለው የሚያስጨንቅ ነገር ስላለ ነው።
#ለመሆኑ_ጭንቀት_ምንድነው?
▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪
⚫ጭንቀት የሰውነትን ተፈጥሯዊ ሚዛን የሚያዛባ የአካል፣የአዕምሮና የስሜት ትንኮሳ የሚፈጥረው ምላሽ፣ ወይም የአንድ ሰው ፍላጎት ሊያንቀሳቅሰው ከሚችለው የግልና የማህበራዊ ሃብቶች አቅም በላይ ሆኖ ሲታየው የሚፈጠር ስሜት፣ ወይም ነገሮች ና ሁኔታዎች ከቁጥጥራችን እንደወጡ ስናስብ የሚፈጠር ስሜት ነው፡፡
⚫ጭንቀት ማለት በስሜትም ሆነ አካለዊ በሆነ መንገድ ሰውነታችን ጠንካራ የአእምሮ ኬሚካሎችን እና ሆርሞኖችን ለማመንጨት የሚገደድበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ጭንቀት ያለመረጋጋት፣ የመረበሽ ወይም የስጋት ስሜትን የሚያካትት ነው።
 ⚫መጨነቅ ተፈጥሯዊ ነው። ሁላችንም የምንኖረው አስተማማኝ ባልሆነ ዓለም ውስጥ በመሆኑ አልፎ አልፎ ማናችንም በጭንቀት ስሜት ልንዋጥ እንችላለን። ጭንቀት በሁሉም ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎችን የሚያጠቃ ነው። መጠኑና ጊዜው ይለያይ እንጂ ጭንቀት የማይነካው ሰው የለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ የሚሉ ለምሳሌ ሰውየው ባለስልጣን ወይም ሀብታም ከሆነ “እንዴት እሳቸው ይጨነቃሉ?” በማለት ሰውየው ከማንኛውም ጭንቀት በየትኛውም ሁኔታና ጊዜ ነፃ ናቸው ብሎ የሚያምኑ ሰዎች አሉት። ሆኖም የትኛውም ሀብት ያለው፣ በየትኛውም እድሜ ክልል ያለውና በየትኛውም የስልጣን እርከን ወይም የሥራ ሃላፊነት ስር ያለው ብንሆንም በጥቂቱም ቢሆን በተለያየ ጊዜና ሁኔታ ጭንቀት አለ። ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊትን ስንመለከት በምዕራፍ 13:2 ላይ “ከሐሳቤ ጋር የምሟገተው፣ ልቤም ቀኑን ሙሉ የሚያዝነው እስከ መቼ ነው?” ሲል ጽፏል። መዝሙር 13፥2 (አዲሱ መ.ት)

 ⚫ጭንቀት በተለይም ወጣቶችን እጅግ የሚያጠቃ ነገር ነው። በዘርፉ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች "ከ18 እስከ 33 አመት ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ከየትኛውም ዕድሜ ክልል ካሉ ሰዎች የበለጠ ጭንቀት አለባቸው። ከ 33 አመት በኋላ የጭንቀት መጠን እየቀነሰ ይሄዳል።" በማለት ይናገራሉ። ሰው በምድር እስካለ ድረስ መጨነቅ በመጠኑም ብሆን አይቀርም።

#የጭንቀት_መንስኤ_ምንድነው?
▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪
⚫የጭንቀት ምክኒያቶች በርካታ ናቸው፡፡  ሆኖም እነዚህ ምክንያቶች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይመደባሉ። እነዚህም አካላዊና ስነ ልቦናዊ ምክንያቶች ናቸው። እነዚህ ምክንያቶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚከተለው እናያለን።
1) የኑሮ ወይም የመሠረታዊ ለፍላጎት ጉዳይ፦ ማቴዎስ 6፥25፤31
⚫ይህ ጉዳይ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ሀገራት ላይ ላሉት ሕዝቦች ዋነኛው የጭንቀት ምንጭ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ በዚህ ጉዳይ የማይጨነቅ ማንም የለም። በእርግጥ መጠኑ ብለያይም።
2) የወደፊት ጉዳይ ወይም ለነገ ማሰብ፦ማቴዎስ 6፥34
⚫በተወሰነ ደረጃ መጨነቅህ ከአደጋ ለመራቅ ንቁ እንድትሆን ያደርግሃል። ደግሞ ለነገ ማሰብ ወይም ስለ ወደፊት ጉዳይ ማሰብ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ይህ ጉዳይ መጥፎ የሚሆነው ሰው ማሰብ ከሚገባው በላይ በማሰብ አሳቡን የጭንቀት ምንጭ ስያደርግ ነው። ስለወደፊቱ ማሰብ በልክና በመጠን ስሆን መልካም ነው። ነገር ግን ከልክና በመጠን ስያልፍ ለጭንቀት ምክንያት ይሆናል።
3) በአንደኛና በሁለተኛ ምክንያቶችን ተከትሎ የሚመጣ አካላዊና ስነልቦናዊ ችግሮች። ለምሳሌ፦
 ✔መሰረታዊ የኢኮኖሚ ግዴታዎችን መወጣት አለመቻል፡- ለምሳሌ የቤት ኪራይ፣ አስቤዛ፣ ወርሃዊ የመብራት ክፍያ ወዘተ…
✔ለአዳዲስ ነገሮች መዘጋጀት፡- ለምሳሌ ቤት መሥራት፣ ትዳር፣ ልጅ መወለድ፣ አዲስን ስራ መያዝ፣ወዘተ
 ✔ከሚወዱት ሰው ጋር የሚፈጠር ችግር
✔ህመም፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ከመጠን ያለፈ አልኮል መጠጣትና ሲጋራ ማጨስ
✔ውጤታማ ያልሆነ ተግባቦት
✔ከመጠን በላይ የሆነ የመረጃ ብዛት
✔ከመጠን ያለፈ የስራ ብዛት ወይም ጫና
✔ጭንቀትን የሚዘሩ ግለሰቦች- በንግግራቸው ሁሉ ጭንቀት የሚፈጥር ወሬን የሚያወሩ (Stress carriers ይባላሉ) እና ወዘተ ናቸው።
4)  የሰይጣን ውጊያና የአከባቢ ተጽዕኖ
⚫ሰይጣን ከላይ በኩል በተዘረዘሩት ምክንያቶችን ተጠቅሞ  ዘወትር መክሰስ፣ ተስፋን ማስቆረጥ፣ እምነት ማሳጣትና በሕይወታቸው ደስተኛ እንዳይሆኑ በማድረግ ሰዎችን ጭንቀታም ያደርጋቸዋል። ከዚህ ጋር ተዳምሮ ደግሞ የአከባቢ ወይም የሰዎች ተጽዕኖ ነገሩን አደገኛ ያደርጋል። ይህን ደግሞ ለከባድ ጭንቀት ምንጭ ይሆናል። 1ሳሙ 1
⚫ሌላው የሰይጣን ውጊያ ደግሞ ከዚህ በፊት በሠሩት ስህተት የተነሳ እንድጨነቁት ማድረግ ዘወትር መክሰስና ማስጨነቅ ነው።

#የጭንቀት_ውጤቶች_ምንድናቸው?
▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪
⚫ጭንቀት አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳትን ያስከትላል። ለምሳሌ ያህል  የሰውነት ድካም፣ ከፍተኛ የራስ ምታት፣ ብስጭት፣ የምግብ ፍላጎት መዛባት፣ የማስታወስ ችሎታ መቀነስ፣ ለራስ የሚሰጥ ዋጋ ወይም ክብር መቀነስ፣ ከማህበራዊ ህይወት መገለል፣ በሽታ አልፎ ተርፎ ነፍስን እስከ ማሳጣት የሚያደርስ አደገኛ ነው። ከዚህም ያለፈ መንፈሳዊ ሕይወታችን በኃይሌና ሁኔታ ይጎዳል። ለመንፈሳዊ ውድቀትም ሊያደርስ ይችላል።

#ጭንቀትን_እንዴት_መቆጣጠር_ይቻላል?
▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪
⚫ጭንቀትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባይቻልም መቆጣጠር ግን ይቻላል። በዕለት ተዕለት ሕይወታችሁ ውስጥ የሚፈጠሩ የውጥረትና የጭንቀት ምንጮችን ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር የሚከተሉትን ስድስት ነገሮችን ተግባራዊ ማድረግ እጅግ በጣም ይጠቅማል።

❶ #የእግዚአብሔርን_መንግሥትና_ጽድቅን_መፈለግ
 ▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪
⚫ተፈጥሮ በሆነ መንገድ መጨነቅ ለሚገባው ነገር በመጠን መጨነቅ አንድ ነገር ሲሆን ጭንቀት ለማያስፈልግ ነገር ከሚገባው በላይ አብልጦ መጨነቅ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ‘ጭንቀት፣ በሚወዛወዝ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ እንደመወዛወዝ ነው’ የሚለውን አባባል ያስታውሰኛል። "ዝም ብለህ ትወዛወዛለህ ግን የትም አትደርስም።”
⚫ሰው ዝንብሎ ለብዙ ነገር ይጨነቃል። ነገር ግን መጨነቅ ለሚያስፈልግ ነገር እንጨነቅ እንጅ መጨነቅ ለማያስፈልግ ነገር ሁሉ መጨነቅ ምንም ጥቅም የለውም። የእግዚአብሔር ቃል በማቴዎስ 6፥27 ላይ “ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?” ይላል።  መልሱ ቀላልና አጭር ነው ማንም። ጭንቀት መፍትሔ የማያስገኝልህ ከሆነ ችግርህን ከማባባስ ወይም ራሱ ችግር ከመሆን ባለፈ የሚፈይድልህ ነገር የለም። ችግሮችን አንድ በአንድ ለመፍታት ሞክር።

⚫አንድ በዘርፉ ጥናት ያካሄደው ባለሙያ “በጥቃቅን ነገሮች ከመጨነቅ ይልቅ በዋናው ነገር ላይ ማተኮር የተሻለ እንደሆነ ተገንዝቤአለሁ። ይበልጥ አስፈላጊው ነገር ምን እንደሆነ ከወሰንኩ በኋላ በዚያ ላይ ትኩረት አደርጋለሁ" ይላል።
⚫ይህ እጅግ በጣም ተገቢና ወሳኝ እርምጃ ነው። የእግዚአብሔር ቃል በፊልጵስዩስ 1:10 ላይ  “ ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ እንድታውቁ፣" ይላል። ይህ ከሁሉ የሚሻለው ደግሞ ምን እንደሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ 6፥33 ላይ “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል።” በማለት ምንን ማስቀደም እንዳለብንና አብልጠን መጨነቅ ያለብን ምን እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል።
⚫ሰው ዘወትር እየተጨነቀ ያለው ለኑሮና ለነፍስ እንጂ ለመንፈስ ማለትም ለእግዚአብሔር መንግሥትና ለጽድቅ አይደለም። ከዚህ ሕይወት ለሰው ልጅ እጅግ በጣም ፈታኝ ሆኗል። የእግዚአብሔር ቃል በማቴዎስ 6፥25፤31 ደግሞ በሉቃስ 12፡22ትም ላይ “ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን?” በአድሱ መደበኛ ትርጉም ደግሞ "ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን?” እያለ ስለነፍስ ወይም ስለኑሮ መጨነቅ እንደሌለብን አስረግጦ ይናገራል። ስለዚህ ስለኑሮ ከማሰብና ከመጨነቅ ይልቅ ለእግዚአብሔር መንግሥትና ለጽድቅ እንጨነቅ። ሌላው ሁሉ ተከትሎ የሚመጣ ተጨማሪ ነገር ነው።

❷ #ጭንቀታችን_በእግዚአብሔር _ላይ_መጣል
 ▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪
⚫የእግዚአብሔር ቃል በ1ኛ ጴጥሮስ 5፥7 ላይ “እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።”ይላል። በዚህ ምድር ስንኖር ብዙ የሚያስጨንቁ ነገሮች ይኖራሉ። ከእኛ የሚጠበቀው ለእርሱ መጨነቅ ሳይሆን ስለእኛ ለሚያስብና ለሚጨነቅ ለአባታችን ለእግዚአብሔር መጣል ነው። “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።”( ኢሳይያስ 41፥10) ያለ አባት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው።
⚫የእግዚአብሔር ቃል በፊልጵስዩስ 4፡4-7 ላይ "ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። … ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” ይላል።
⚫ስለዚህ እኛ ላለመጨነቅ ጭንቀታችን በእግዚአብሔር ላይ መጣል አለብን። አለዚያ እኛ ስለራሳችን እንጨነቃለን፣ ስለራሳችን እናስባለን በስተመጨረሻ ራሳችንን እንጎዳለን። ከዚህ አልፎ ለምድር ኑሮ ብቻ እያሰብን ከእግዚአብሔር መንግሥትም ጭምር ልንርቅ እንችላለን። ስለዚህ ሃሳባችንና ጭንቀታችን በፀሎት ለእርሱ በመጣል የእረፍት ሕይወት እንኑር።

❸ #ለነገ_አለመጨነቅ
▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪▪
⚫የእግዚአብሔር ቃል በማቴዎስ 6፥34 ላይ “ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።” በአድሱ መደበኛ ትርጉም ደግሞ “ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና”።” ይላል። የነገን ችግር ዛሬ ላይ አምጥተህ የምትጨነቅ ከሆነ ምንም ትርጉም የለውም፤ የተጨነቅንበት አንዳንዱ ነገር ጭራሽ ላይከሰት ይችላል። ልትለውጠው የማትችለውን ነገር አምነህ ተቀበል። አንድ ሰው እንዲህ በማለት ይናገራል “ከሁሉ የተሻለው ነገር ለሚያጋጥሙህ ነገሮች ራስህን ማዘጋጀት ነው፤ ሆኖም አንዳንድ ነገሮች ከአንተ ቁጥጥር ውጭ እንደሆኑ አምነህ ተቀበል።”
⚫የእግዚአብሔር ቃል በመክብብ 9፥11 ላይ “ሌላም ነገር ከፀሓይ በታች አየሁ፡ ሩጫ ለፈጣኖች፣ ውጊያም ለኀያላን አይደለም፤ እንጀራ ለጥበበኞች፣ ወይም ባለጠግነት ለብልሆች፣ ወይም ሞገስ ለዐዋቂዎች አይሆንም፤ ጊዜና ዕድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል።”ይላል። ፈጣኖች በውድድር ሁልጊዜ አያሸንፉም፤ . . . እውቀት ያላቸው ሰዎችም ሁልጊዜ ስኬታማ አይሆኑም፤ ምክንያቱም ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ያለህበትን ሁኔታ መለወጥ አትችል ይሆናል፤ ስለ ጉዳዩ ያለህን አመለካከት ግን መለወጥ ትችላለህ።
⚫ ለነገ አትጨነቅ ማለት አታስብ ወይም አትስራ ማለት ሳይሆን ለነገ በማሰብ አትጨነቅ ማለት ነው። ነገ ምን እሆናለሁ? ነገ ምን እበላለሁ፣ ምን እጠጣለሁ፣ ምን እለብሳለሁ ወዘተ በማለት አለመጨነቅ ነው። ነገር ግን ለነገ ማሰብና ማቀድ ጠንክሮ መስራት፣ መቆጠብና ባለጠጋ መሆን ይቻላል።  “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ” (1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥6) እንደሆነ ደግሞ መርሳት የለበትም። አንድ ሰው ይህን እውነት ከተረሳና ከቃሉ ውጭ ከሆነ ባለጠጋ ለመሆን ባለው ከፍተኛ ፍላጎትና ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚመጣ ገንዘብ መውደድ ተታልሎ ምናልባት ኃይማኞትን እስከ መካድ ልደርስ እንደሚችል የእግዚአብሔር ቃል በ1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡9-10 ላይ " ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።" እያለ ይናገራል።

❹ #ጭንቀታችን_ለቤተሰብን_ወይም_ለጓደኛን_ማማከር።
⚫የእግዚአብሔር ቃል በምሳሌ 12፥25 ላይ “ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል” ይላል። ይህ ማለት ጭንቀትህ ቀለል እንዲልህ የሚረዱ ጠቃሚ ምክሮችን ከወላጅህ ወይም ከጓደኛህ ማግኘት ትችላለህ ማለት ነው። የልብህን ሀዘንና ጭንቀትን ለሌሎች ማካፈል በመጠኑም ብሆንም ጭንቀቱን ቀለል ያደርጋል።
⚫ጭንቀት መውጫ ቀዳዳ የሌለው በሚመስል አሉታዊ አስተሳሰብ አእምሮህ እንዲወጠር ሊያደርግ ይችላል። ጭንቀት መውጫ የሌለው ሁኔታ ውስጥ እንዳለህ ሆኖ እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል፤ አንተ ካለህበት ሁኔታ ውጭ ያለ ሰው መውጫውን ሊጠቁምህ ይችላል። ስለዚህ ጭንቀትን ለሌሎች ማለትም ቅርብ ለሆኑ ሰዎች አካፍል።
⚫ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ስሜታዊ ውጥረትን የመቋቋም ችሎታቸው ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ ሊሆን የቻለበት አንድ ምክንያት ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ከጓደኞቻቸው ጋር ጥብቅ ቅርርብ እና ጓደኝነት ስለሚመሰርቱ ነው፡፡ ስለዚህ፣ በስራም ሆነ በሌላ ጉዳይ አእምሮ ውጥር ሲል ባልንጃራን/ጓደኛን አግኝቶ የሆድ የሆድን ማውራት “እፎይ” ለማለት ይረዳል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “የሰከነ ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” በማለት ይገልጻል። ( ምሳሌ 14:30 ) በሌላ በኩል ደግሞ


❺ #በመሰጠት
 ⚫የእግዚአብሔር ቃል በሉቃስ 6፥38 ላይ “ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል።” ይላል። መስጠት ጤናን ለመጠበቅም የሚረዳ የጭንቀት መድኃኒት ነው። ህይወታችን በትርጉም የተሞላና በዓላማ የታጠረ እንዲሆን ያግዛል፡፡ ስለዚህ፣ ያላችሁን ማንኛውንም ነገር ጊዜም ሆነ ገንዘብ እንደየአቅማችሁ እና ነባራዊ ሁኔታችሁ ስጡ፣ በምትኩ ከውጥረት ነፃ የሆነ ህይወት ይሰጣችኋል፡፡
⚫አንድ አንዶቻችሁ እዚህ ጋር “እኔ ራሴ እርዳታ የምፈልግ ሰው ነኝ፡፡ ምን ኖሮኝ ነው የምሰጠው? ራስ ሳይጠና…፡፡” ትሉ ይሆናል፡፡ ጊዜን መስጠት፣ ጉልበትን መለገስ፣ አከባቢን ፅዱና አረንጓዴ ማድረግ ወዘተ በነፃ ራስ ሳይጠናም በዙሪያችን ለሚገኙ ሰዎች ልናበረክት ከምንችለው ብዙ ነገር መካከል ጥቂቱ ነው፡፡ እና ነገሩ “ከአንጀት ካለቀሱ” ነውና እንዲያው ለሌሎች ብቻ ብለን ሳይሆን ለራሳችንም አሰብ አድርገን መስጠትን ባህላችን እናድርግ፡፡

❻ #ባለው_መደሰትና_ዜና_ማለት
⚫በየዕለቱ ዘና ሊያደርገን የሚችል አንድ ነገር ማድረግ መቻል ውጥረትን መቀነሻ ፍቱን መላ ነው፡፡ በመዘሙር እግዚአብሔርን ማምለክ፣ የእግዚአብሔር ቃልን ማንበብ፣ ከቅዱሳን ጋር ሕብረት ማድረግና መጫወት፣ በተገቢው ሁኔታ መዝናናት እና ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ ምንም ይሁን ምን በየዕለቱ አንድ ዘና የሚያደርጋችሁን ነገር ማድረግ ውጥረትን ለመቀነስም ሆነ ለመቆጣጠር በእጅጉ ይረዳል፡፡ የሚያስደስታችሁን ነገር በየጊዜው ባደረጋችሁ ቁጥር ለምትሰሩትም ስራ የሚኖራችሁ ፍቅር እንዲሁ ተያይዞ እየጨመረ ይሄዳል፡፡
⚫በየቀኑ መጠነኛ ፋታ የምታገኙበት ጊዜ ይኑራችሁ፡፡ በዚህ የፋታ ሰዐታችሁ ታዲያ ከየትኛውም አይነት ሀላፊነት እና ተግባር ራሳችሁን ነፃ በማድረግ አእምሮአችሁንም ሆነ አካላችሁን ለማሳረፍ ሙከራ አድርጉ፡፡ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና ታሸንፋላችሁ።

Comments

Popular posts from this blog

መንፈሳዊ አገልግሎት

3ቱ የክርስቲያን ልብሶች

መንፈሳዊ እርጅና