የአገልግሎት ትክክለኛ ምንነት ማወቅና መኖር

የአገልግሎት ትክክለኛ ምንነት ማወቅና መኖር 

1.የትምህርቱ አስፈላጊነት 
ትምህርቱ ለምን አስፈላጊ ሲባል መንፈሳዊ ሕፃንነት በተለይም የአገልግሎት ምንነትና ትርጉም በትክክል ያለማወቅ፤ አውቆም በትክክል  ያለመኖር ችግር ጎልቶ እየታየ ስላለ በአገልግሎት ምንነት ዙሪያ በተወሰነ መልክ ግንዛቤ ለመስጠት ነው።
1ኛ ቆሮንቶስ 3፥1 “እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም።” 
ዕብራውያን 5፥12-14 "ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።

2.የትምህርቱ ዓላማ
የትምህርቱ ዓላማ፦ እያንዳንዱን የኳይር አባል ከመንፈሳዊ ሕፃንነትን በማላቀቅ ወደ መንፈሳዊ ብስለት ማሸጋገርና የአገልግሎትን ትክክለኛ ምንነትና ትርጉም በሚገባ እንዲረዱ ማድረግ ነው።

3.የትምህርቱ ግብ
የትምህርቱ ግብ፦ እያንዳንዱ የኳይር አባል ከመንፈሳዊ ሕፃንነት ተላቆ የአገልግሎትን ትክክለኛ ምንነትና ትርጉም በሚገባ ተረድተው እውነተኛ አገልጋይ ሆኖ ሲገን ማየት ነው።

 1. የአገልግሎት ምንነት 
1.አገልግሎት እድል ነው።
◈አገልግሎት የሰማይና የምድር ጌታ የሆነውን ታላቁን እግዚአብሄርን ለማገልገል የተሰጠ እድል ነው፡፡
ዘኍልቁ 16፥9 “የእስራኤል አምላክ ከእስራኤል ማኅበር የለያችሁ፥ የእግዚአብሔርንም ማደሪያ አገልግሎት ትሠሩ ዘንድ፥ እንድታገለግሉአቸውም በማኅበሩ ፊት ትቆሙ ዘንድ ወደ እርሱ ያቀረባችሁ አይበቃችሁምን?”  
2 ዜና 29፥11 “ልጆቼ ሆይ፥ በፊቱ ትቆሙና ታገለግሉት ዘንድ፥ አገልጋዮቹም ትሆኑ ዘንድ፥ ታጥኑለትም ዘንድ እግዚአብሔር መርጦአችኋልና ቸል አትበሉ።”

◈ስለዚህ ሁልጊዜም እግዚአብሔርን ልናገለግል ስንነሳ ከምድር ላይ ካሉት ሕዝቦች በሙሉ በመለየት እግዚአብሔርን እናገለግለው ዘንድ እድሉን እንዳገኘን ማሰብና መቁጠር አለብን፡፡ ለአገልግሎት ስንነሳም ራሳችንን ትልቅ እጣ እንደወጣለት እድለኛ ሰው መቁጠርና ማየት አለብን፡፡
ገላትያ 1፥15-16 "ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥" 

2. አገልግሎት ስራ ነው።
◈አገልግሎት የሰማይና የምድርን ጌታ ከሆነው ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ለተመረጡት ወይም እድለኛ ለሆኑት የተሰጠ መንፈሳዊ ስራ ነው። 
ፊልጵስዩስ 2፥25፤30 “ነገር ግን ወንድሜንና ከእኔ ጋር አብሮ ሠራተኛ ወታደርም የሚሆነውን፥ የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን አፍሮዲጡን እንድልክላችሁ በግድ አስባለሁ፤ ....በእኔ ዘንድ ካላችሁ አገልግሎት እናንተ ስለሌላችሁ የጎደለኝን እንዲፈጽም፥ በነፍሱ ተወራርዶ ከጌታ ሥራ የተነሣ እስከ ሞት ቀርቦአልና።” 
ፊልጵስዩስ 2፥30 (አዲሱ መ.ት) “እርሱም እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት ለማሟላት ሲል ለሕይወቱ እንኳ ሳይሳሳ፣ ለክርስቶስ ሥራ ከሞት አፋፍ ደርሶ ነበርና።” 

✅አገልግሎት ስራ ነው ሲባል ዕለታዊ እንጀራ ለማግኘት ብቻ ወይም ሰዎች ስላዘዙ ብቻ ወይም ሰዎች ስለፈለጉ ብቻ ወይም ደግሞ መርሐ ግብር ፕሮግራም ለመፈጸምና ለማስፈጸም ያህል ብቻ የምንሰራው ስራ አይደለም። 

✅አገልግሎት ስራ ነው ሲባል፦
➤ ከእግዚአብሔር ጸጋና ምሕረት የተነሳ ጌታን እንደ ግል አዳኛቸው አድርጎ የተቀበሉት እንዲሠሩት የተሰጠ መንፈሳዊ ስራ ነው።
➤ በአማኞች በጎ ፈቃደኝነት ላይ ተሰማርቶ የምሠራ መንፈሳዊ ተግባር ነው።
➤ አማኞች ገና እንዲባረኩ ሳይሆን ስለተባረኩ የሚሠሩት ቅዱስ ተግባር ነው።
➤ የአገልግሎቱ ባለቤት ታማኝ አድርጎ በቆጠራቸው ላይ ጌታ ያኖረው ውድና ክብር መንፈሳዊ አደራ ነው።
➤ አገልጋዩ ተልዕኮውን የሚፈጸምበትና ጸጋውን ለሌሎች የሚያስተላልፍበት መንገድ ነው።

✅አገልግሎት ስራ በመሆኑ በውስጡ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን አሉ፡፡ በመሆኑም ይህንን የእግዚአብሄር ስራ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ ሳንታክት በኃይልና በብርታት እንዲሁ በትጋት መስራት ወይም ማገልገል ያስፈልጋል፡፡
“2ኛ ቆሮ 4፥1 ስለዚህ ምክንያት ምሕረት እንደ ተሰጠን መጠን ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም።” 

3. አገልግሎት ውጊያ ነው።
◈አገልግሎት እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነን፥ መከራ የምንቀበልበት፣ ስለ ክርስቶስ የምንዋጋበት መንፈሳዊ ውጊያ ነው (2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥3)።
◈አገልግሎት ውጊያ የሚሆነው እንዴት ነው ሲባል በጎች ሆነን ወደ ተኩላዎች መካከል ስለምንላክ ነው።
ማቴዎስ 10፥16-19 "እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ። ነገር ግን ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ በምኩራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤ ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፥ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ።"

◈አንድ አገልጋይ በአገልግሎት ዘመኑ ከሦስት ነገሮች ጋር ውጊያ ይገጥማል። እነርሱ ከሰይጣን፣ ከራስ ማንነትና ከራስ ሰዎች (ቤተሰብ፣ጓደኛ) ጋር ነው። አንድ አገልጋይ እነዚህ ጠላቶችሁን ማሸነፍ አለበት። 

4.አገልግሎት አምልኮ ነው።
◈አገልግሎት አምልኮ ነው፡፡ አምልኮ ደግሞ ለእግዚአብሄር ብቻ የሚሰጥና ሰው የተጠራበት ትልቁ ዓላማ ነው።
“ዘጸአት 4፥23  "እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ ይገዛልኝ ዘንድ ልጄን ልቀቅ” 
ዘጸአት 7፥16 “እንዲህም ትለዋለህ፦ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር፦ በምድረ በዳ እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ።” 
ዘጸአት 8፥1 “እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው፦ ወደ ፈርዖን ግባ እንዲህም በለው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።” 

6. አገልግሎት ፍቅር ማሳያ መድረክ ነው።
◈አገልግሎት ለእግዚአብሄር ያለንን ፍቅር፣ ለእግዚአብሄር ያለንን መውደድ የምንገልጥበት መድረክ ነው፡፡ 
ኢሳይያስ 56፥6 “ያገለግሉት ዘንድ የእግዚአብሔርንም ስም ይወድዱ ዘንድ ባሪያዎቹም ይሆኑ ዘንድ ” 


2. የአገልጋይ ምንነት 
✅የአገልጋይ ጥሬ ትርጉም ባሪያ፣ ታዛዥ ወይም አሽከር የሚል ሲሆን በእግዚአብሔር ቃል አንጻር አገልጋይ ማለት፦

1ኛ. በእግዚአብሔር የተመረጠና በጌታ መንፈሳዊ ሥራ ላይ የተወከለ መንፈሳዊ ሰው ነው። 
2ኛ. የእግዚአብሔር አሳብ፣ ዓላማና ፕሮግራም የሚከናወንበት መጠቀሚያ ዕቃ ነው።
3ኛ. እግዚአብሔር ራሱን ለሰዎች የሚገልጥበት መሣሪያ ነው።
4ኛ.ጌታው ለእርሱ የከፈለው መሥዋዕትነትና ውለታ አስበው ጌታ የሚያዘውን በታማኝነት ለመታዘዝ የተሾመ ሰው ነው።
5ኛ. በጌታ ቤት ወይም በቅዱሳን መካከል የጌታ ሥራ እንዳይቀዘቅዝና እንዳያቋርጥ የተቻለውንና ተገቢውን ጥረት የሚያደርግ የጌታ ታማኝ ባሪያ ነው።




3. ከአንድ አገልጋይ ምን ይጠበቃል?
1ኛ. የተለወጠ ማንነት
✅መለወጥ ሲባል ከአሮጌው አዳማዊ ባሕሪያችንና ሥራችን መላቀቅ እንዲሁም ከልጅነት ፀባይ፣ አስተሳሰብና አመለካከት መውጣት ማለት ነው።
ፊልሞና 1፥10-11 “አስቀድሞ ስላልጠቀመህ፥ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ።” 

2ኛ. ፍቅርና ቅድስና
✅ፍቅርና ቅድስና ትልቁና ዋነኛው የአገልጋይ ባሕርይ/ quality ነው። ፍቅርና ቅድስና የአገልግሎት መሠረት ናቸው። ከሁለቱ ውጭ የሆነ የትኛውም አገልግሎት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ከንቱ አገልግሎት ነው።
3ኛ. ትሕትና መታዘዝ 
✅ትሕትና መታዘዝ ሌላው ወሳኝ አገልጋይ ባሕርይ ነው። ትህትና መታዘዝም ልክ እንደ ፍቅርና ቅድስና የአገልግሎት መሠረት ነው፡፡ ከሁለቱ ውጭ የሆነ ማነኛውም አገልግሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ ቢስ የሆነ እንዲሁም ዋጋ የሚያስከፍል አደገኛ አገልግሎት ነው።
4ኛ. ኃላፊነት ወይም ሸክም
✅አንድ አገልጋይ ለአገልግሎቱ ሸክም ያለው ኃላፊነት የሚሰማው፣ ለአገልግሎቱ ግድ የሚለው መሆን አለበት። ይህ ባሕርይ የሌለው ማለትም ለአገልግሎት ምንም ሸክም የማይሰማው፣ አገልግሎቱን በግራ እጅ የሚይዝ ግድየለሽ የሆነ አገልጋይ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጣለ፤ በአገልግሎቱም መርገምን እየሰበሰበ ያለ አገልጋይ ነው።
2ኛ ቆሮ 11፥28 “የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።” 

5. መሰጠት 
✅እግዚአብሔር ከአንድ አገልጋይ በጣም የሚፈልገው ነገር ቢኖር መሰጠት ነው። መሰጠት ሲባል አጠቃላይ ሁለንተናን ለእግዚአብሔር መሰጠት ነው። 
2ኛ ቆሮ 8፥5 “አስቀድመውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለጌታ ለእኛም ሰጡ እንጂ እንዳሰብን አይደለም።” 

✅ለእግዚአብሔር በሙሉ ማንነት ያልሰጠ አገልጋይ መስቀሉን ተሸክሞ ዘወትር ኢየሱስን መከተል አይችልም። እንድ ዓይነት አገልጋይ ደግሞ ለጌታ ልሆን አይገባውም። 
ማቴዎስ 10፥38 “መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።” 

6ኛ. ትጋት 
✅የአንድ አገልጋይ ትልቁ መለያ ትጋት ነው። ትጋት የሌለው ወይም የማይተጋ ሰነፍና እንቅልፋም አገልጋይ፤ አገልጋይ መሆን ይቅርና አገልጋይ ልባልም አይገባም።
ቆላስይስ 3፥23-24 "ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥ ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና።"

7ኛ. ታማኝነት
✅ከአንድ አገልጋይ እግዚአብሔር ታማኝነት ይፈልጋል። አንድ አገልጋይ ለአገልግሎቱ ለሾመው ደግሞ ታማኝ አድርጎ ለቆጠረው ለእግዚአብሔር (“ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረኝ፥"1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥12) ለሁሉም አቅጣጫ ታማኝ መሆን አለበት፤ እንዲሁም ለሰው ታማኝ መሆን አለበት። አለዚያ ለእግዚአብሔር የሚያሳፍር ሠራተኛ ይሆናል። ለዚህ ነው ሐዋሪያው ጳውሎስ ልጁን ጢሞተዎስን 
በ2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥15 ላይ፤ “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፥ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ።” የሚለው።


ማጠቃለያ፦
 ዕብራውያን 6፥1-2  “ስለዚህ የክርስቶስን ነገር መጀመሪያ የሚናገረውን ቃል ትተን ወደ ፍጻሜ እንሂድ፤ መሠረትን ደግመን አንመሥርት፥ እርሱም ከሞተ ሥራ ንስሐና በእግዚአብሔር እምነት፥ ስለ ጥምቀቶችና እጆችንም ስለ መጫን ስለ ሙታንም ትንሣኤ ስለ ዘላለም ፍርድም ትምህርት ነው።” 

Comments

Popular posts from this blog

መንፈሳዊ አገልግሎት

3ቱ የክርስቲያን ልብሶች

መንፈሳዊ እርጅና