በራስ ማስተዋል አትደገፍ
በራስ ማስተዋል መደገፍ የሰው ልጆች ችግር ሥር ከመሆኑ ባሻገር ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ ለሚያደርጉት አመፅ ዋነኛ አነሳሽ ምክንያት እና ሰይጣን ሰዎችን ለማጥመድ ከሚጠቀምባቸው ዋነኛና መንገዶች አንዱ ነው። ይህም የሰይጣን ዋነኛ የውጊያ ስልት ነው።
የሰይጣን ዋነኛ የውጊያ ስልት፣ ሰዎች በእግዚአብሔር ባሕሪ ላይ ያላቸውን እምነት በመሸርሸር እግዚአብሔር ሊታመን የማይችል አምላክ እንደሆነ ማሳመን እና በራሳቸው ማስተዋል ላይ እንዲደገፉ ማግባባት ነው (ዘፍ.3፥1-5)።
ይህንንም የሚያደርገው የእግዚአብሔር ባህሪ አጣሞ፣ ቀይሮ እና አወናብዶ በማስቀመጥ፣ ውሸትን እውነት አስመስሎ በማቅረብ ለሚሰሙት ሁሉ በመስበክ፣ የተዘራውን እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል በመንጠቅ፣ በማታለል እና የመሳሰሉትን የማወናበድ ስራዎች በመስራት ነው።
ለአብነት በዘፍ. 3፥1-5 ላይ ተመዝግቦ ባለው የአዳምና ሔዋን ታሪክ ውስጥ ሰይጣን፣ እግዚአብሔር ከአዳምና ሔዋን አንዳች የሚጠቅም ነገር የደበቀባቸው፣ የእነርሱን መልካም ነገር የማይሻ፣ እና ሊታመን የማይችል አምላክ መሆኑን በእጅ አዙር ነግሮና በውስጣቸው ጥርጥርን ዘርቶ እግዚአብሔርን ውሸታም ለማድረግ ያደረገውን ሴራ እናያለን፡፡
ሴራም እንዲሁ በከንቱ አልቀረምና ተሳክቶለት አዳምና ሔዋን በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን መደገፍ ወደጎን በመተው፣ በራሳቸው ላይ በመተማመን፣ ሰይጣን በእግዚብሔር ባሕሪ ላይ የተናገረውን የውሸት ቃል አደመጡ፡፡ ከእግዚአብሔር ውጪም በራሳቸው ማስተዋል በመደገፍ በራሳቸው መንገድ ተራመዱ። በስተመጨረሻም በእግዚአብሔር ላይ ካላቸው መታመን ወጡ።
አዳምና ሔዋን በእግዚአብሔር ላይ ካላቸው መታመን መውጣታቸውን የሚያመላክቱ ሦስት ማሳያዎች አሉ፡፡ እነዚህም (1) የሰው ማስተዋል (ለጥበብ መልካም እንደሆነ አዩ)፣ (2) የሰውነት ፍላጎት (ለመብላት ያማረ እንደሆነ አዩ)፣ እና (3) ገንዘብ ማድረግ ወይም የራስ ማድረግ (ለዓይን እንደ ሚያስጎመጅ አዩ)፡፡
ዛሬም የዘወትር ፈተናዎቻችን ከነዚህ በአንዱ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ በራስ ማስተዋል መደገፍ የሰው ልጆች ችግር ሥር ከመሆኑ ባሻገር ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ ለሚያደርጉት አመፅ ዋነኛ አነሳሽ ምክንያት እና ሰይጣን ሰዎችን ለማጥመድ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች ዋነኛና መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡
በአጠቃላይ ኃጢአቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ካለመታመን ወይም በራስ ማስተዋል ከመደገፍ ይመነጫሉና በዚህ አደገኛ መንፈስ እንዳንጠቃ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ለዚህም የኢየሱስን ፈለግ መከተል ያስፈልገናል።
ኢየሱስም አዳም እንደ ተፈተነ በተመሳሳይ ሦስት አቅጣጫዎች ላይ ተፈተነ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ሰይጣን ያቀረበለትን በራስ የመታመን ግብዣ ወደጎን በመተው ራሱን በእግዚአብሔር ጥበቃ ስር አሳልፎ በመስጠት ለመኖር ወሰነ (ማቴ. 4:1-10)፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ፈጽሞ በመደገፍ ሊኖር የሚችለውንም የድል ሕይወት ኖሮ አሳየን።
እኛም ዛሬ ኢየሱስ የኖረውን የድል ሕይወት ለመኖር በራሳችን ማሰተዋል ከመደገፍ ወጥተን በእግዚአብሔር ላይ በፍጹም ልባችን መታመን ያስፈልጋል። “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤” ምሳሌ 3:5
ሰይጣን "አንተ በራስህ የሆነ ነገር ማድረግ ትችላለህ" ስልህ "እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም" በማለት መልስ። እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና (ዮሐ. 5፥30)።
ሰይጣን "የራስህን ፈቃድህን ማድረግ ትችላለህ" ስልህ እኔ "የራሴን የጌታን ፈቃድ እንጂ የራሴን ፈቃድ ለማድረግ አልመጣሁም" በማለት መልስ። ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና (ዮሐ. 6፥38)።
🔖እነዚህንና የመሳሰሉት ምላሾች በመመለስ የሰይጣንን ውጊያ ማሸነፍና በእግዚአብሔር ላይ ያለውን መታመን ማሳደግ እንችላለን።
Good bless u more than this way man of God im proud of u keep up continue
ReplyDelete