በራስ ማስተዋል አትደገፍ
በራስ ማስተዋል መደገፍ የሰው ልጆች ችግር ሥር ከመሆኑ ባሻገር ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ ለሚያደርጉት አመፅ ዋነኛ አነሳሽ ምክንያት እና ሰይጣን ሰዎችን ለማጥመድ ከሚጠቀምባቸው ዋነኛና መንገዶች አንዱ ነው። ይህም የሰይጣን ዋነኛ የውጊያ ስልት ነው። የሰይጣን ዋነኛ የውጊያ ስልት፣ ሰዎች በእግዚአብሔር ባሕሪ ላይ ያላቸውን እምነት በመሸርሸር እግዚአብሔር ሊታመን የማይችል አምላክ እንደሆነ ማሳመን እና በራሳቸው ማስተዋል ላይ እንዲደገፉ ማግባባት ነው (ዘፍ.3፥1-5)። ይህንንም የሚያደርገው የእግዚአብሔር ባህሪ አጣሞ፣ ቀይሮ እና አወናብዶ በማስቀመጥ፣ ውሸትን እውነት አስመስሎ በማቅረብ ለሚሰሙት ሁሉ በመስበክ፣ የተዘራውን እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል በመንጠቅ፣ በማታለል እና የመሳሰሉትን የማወናበድ ስራዎች በመስራት ነው። ለአብነት በዘፍ. 3፥1-5 ላይ ተመዝግቦ ባለው የአዳምና ሔዋን ታሪክ ውስጥ ሰይጣን፣ እግዚአብሔር ከአዳምና ሔዋን አንዳች የሚጠቅም ነገር የደበቀባቸው፣ የእነርሱን መልካም ነገር የማይሻ፣ እና ሊታመን የማይችል አምላክ መሆኑን በእጅ አዙር ነግሮና በውስጣቸው ጥርጥርን ዘርቶ እግዚአብሔርን ውሸታም ለማድረግ ያደረገውን ሴራ እናያለን፡፡ ሴራም እንዲሁ በከንቱ አልቀረምና ተሳክቶለት አዳምና ሔዋን በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን መደገፍ ወደጎን በመተው፣ በራሳቸው ላይ በመተማመን፣ ሰይጣን በእግዚብሔር ባሕሪ ላይ የተናገረውን የውሸት ቃል አደመጡ፡፡ ከእግዚአብሔር ውጪም በራሳቸው ማስተዋል በመደገፍ በራሳቸው መንገድ ተራመዱ። በስተመጨረሻም በእግዚአብሔር ላይ ካላቸው መታመን ወጡ። አዳምና ሔዋን በእግዚአብሔር ላይ ካላቸው መታመን መውጣታቸውን የሚያመላክቱ ሦስት ማሳያዎች አሉ፡፡ እነዚህም (1) የሰው ማስተዋል (ለጥበብ መልካም እንደሆነ አዩ...